Welcome to
Announcement መቶ ዓመት ታሪክ፤ መቶ ዓመት ክብር"፤ የታሪካዊው ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከበረ

መቶ ዓመት ታሪክ፤ መቶ ዓመት ክብር"፤ የታሪካዊው ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከበረ

28th April, 2026

መቶ ዓመት ታሪክ፤ መቶ ዓመት ክብር"፤ የታሪካዊው ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመቶኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከበረ 


አዲስ አበባ | ሚያዝያ 19/ 2018 ዓ.ም


ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ፋና ወጊ የሆነውና "የአፍሪካው ሃርቫርድ" በመባል የሚታወቀው ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ የመቶኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መዝጊያ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በደመቀ ሁኔታ አክብሯል ።


በዓሉ ልዩ የሚያደርገው ለበርካታ ዓመታት "እንጦጦ" በሚል ስያሜ ሲጠራ የቆየው ተቋም፣ ታሪካዊና ትክክለኛ ማንነቱን መልሶ "ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ" ተብሎ በይፋ የተሰየመበት ዕለት በመሆኑ ነው ። 

✍️ የታሪክ ፍትህና የልህቀት ጉዞ

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ በቢሮ ሀላፊ ደረጃ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና ኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መደክሳ ከበደ እንደገለጹት፤ ይህ ግቢ ከዛሬ አንድ ክፍለ ዘመን በፊት ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. በልዑል ተፈሪ መኮንን ሲመረቅ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ አቅጣጫ ያስቀየረ የታሪክ አውድማ ነበር ። ተቋሙ ዛሬ ወደ ቀድሞ ስሙ መመለሱ የታሪክ ፍትህ መረጋገጡን የሚያሳይ ሲሆን፣ ለዚህም የቀድሞ ተማሪዎች (Alumni) ላለፉት 25 ዓመታት ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ምስጋና አቅርበዋል ። 


ኃላፊው አክለውም፣ ተቋሙ በታሪካዊው ቀን የትምህርት ጥራት አስተዳደር ሥርዓቱን ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ለማድረስ ባደረገው ጥረት የ ISO 21001:2018 (EOMS) የምስክር ወረቀት በይፋ መረከቡን ገልጸዋል ። ይህም ተማሪዎች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደ "ፓስፖርት" የሚያገለግል መሆኑን አስረድተዋል ።

✍️ የነገው መቶ ዓመት ራዕይ

የኮሌጁ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የመቶኛ ዓመት በዓል ትናንትን መዘከር ብቻ ሳይሆን የነገውን መቶ ዓመት ራዕይ የምንሰንቅበት ነው ብለዋል ። ኮሌጁ አሁን ካለበት ደረጃ ተሻግሮ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) እንዲሆን ታላቅ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል ።ዲኑ እንደተናገሩት፣ የቀድሞ ተማሪዎች ለተቋሙ ዕድገት የጀርባ አጥንት በመሆን የጂ 3 (G+3) ሕንፃ ግንባታ እና የላቦራቶሪ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ። ይህንን ትስስር ለማጠናከርም "የቀድሞ ተማሪዎች ቀን" በየዓመቱ እንዲከበርና ቋሚ ቢሮና የመገናኛ ክለብ በግቢው ውስጥ እንዲመሰረት መወሰኑን አብስረዋል ።

✍️ቴክኖሎጂ ለሀገር ብልጽግና

በዓሉ በከተማ አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ ከሚከበረው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ጋር ተያይዞ የተከናወነ ሲሆን፣ "የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የፈጠራ ውጤቶች አውደ-ርዕይ ቀርቧል ። በዚህም በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተሠሩ፣ ገበያን የሚመጥኑና የኢንዱስትሪውን ችግር የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታ በቅተዋል ።ተፈሪ መኮንን ኮሌጅ ባለፉት መቶ ዓመታት እንደ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ-ወልድ፣ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ እና ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ያሉ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንን ያፈራ የታሪክ ፋብሪካ መሆኑ ተገልጿል ። በዓሉም "መቶ ዓመት ታሪክ! መቶ ዓመት ክብር!" በሚል መሪ ቃል በቴያትር፤ በፋሽን ሾዉ፤ በሙዚቃ ፤ በስእል አርት እና በቴክኖሎጂ ኢግዚብሽን ወ.ዘ.ተ ትዕይንቶች በደመቀ ሁኔታ ተጠናቅቋል። 

.

Copyright © All rights reserved.