የ16ኛው ቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከተማ አቀፍ የሰልጣኞች የክህሎት ውድድር <<የቴክኖሎጂ ፈጠራ፤ለሀገር ምጥቀትና ብልፅግና>> በሚል መሪ ሀሳብ ተካሄደ።
🇪🇹 የካቲት 25/2018 ዓ.ም 🇪🇹
በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት በየአመቱ የሚካሄደው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በተያዘው የ2018 በጀት ለ16ኛ ጊዜ በተለያዩ ሁነቶች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በቴክኒክና ሙያ ሳምንቱ ከሚካሄዱ ሁነቶች አንዱ የሆነው እና በቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች መካከል የሚካሄደው የሰልጣኞች ከተማ አቀፍ የክህሎት ውድድር <<የቴክኖሎጂ ፈጠራ፤ለሀገር ምጥቀትና ብልፅግና>> በሚል መሪ ሀሳብ በምርታማነት ማሻሻያና ልህቀት ማዕከል ተካሂዷል።
ውድድሩ የሚሰሩ እጆችና የሚያስቡ አዕምሮዎችን ክህሎት በማስታጠቅ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የጠቀሱት የምርታማነት ማሻሻያና ልህቀት ማዕከል ዋና ዲን አቶ አድማሱ በቀለ ሰልጣኞች ብቃትና ተወዳዳሪነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት መርሃ-ግብር ነው ብለዋል።
በተለይም ከ12ኛ ክፍል ውጤት በኋላ ወደ ዘርፉ ለሚመጡ ወጣቶች እንደ ማነቃቂያና ማሳያ ከመሆኑም ባለፈ ሰልጣኞች ለስራ ፈጠራና ለቀጣይ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ዝግጁነት የሚያረጋግጡበት ትልቅ መድረክ ነው።
በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና ኢንኩቤሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ በየነ በበኩላቸው የውድድሩ ዋነኛ ፋይዳ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና የሰልጣኞችን የወደፊት የሥራ ዕድል የሚወስን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ውድድሩ በሀገሪቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ የተቀመጡትን የኢኮኖሚ ዕድገት ግቦች ለማሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን ሰልጣኞች በክህሎታቸው ተወዳድረው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡና እንደ 15ኛው ቴክኒክና ሙያ ሳምንት የክህሎት ውድድር አሸናፊዎች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በመርሃ-ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ተወዳዳሪ ሰልጣኞች የሚያሳዩት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሀገር ብልጽግናና ዕድገት እንዲውል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ ቀርቧል።
በተያያዘም አወዳዳሪ ዳኞች በከተማ ደረጃ የሚካሄደውን ውድድር በፍትሃዊነትና እንዲመሩ እና ሰልጣኞችም በውድድሩ ወቅት አስፈላጊውን የሥነ-ምግባር ደንብ በመከተል እንዲወዳደሩ መመሪያ ተሰጥቷል።
ውድድሩ በተጠሪ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በ20 የሙያ አይነቶች 509 ሰልጣኞችን በማሳተፍ የተጀመረ ሲሆን በየደረጃው በነበሩ ማጣሪያዎች ያለፈ ነው።
በክላስተር ደረጃ 123 ሰልጣኞች ከተወዳደሩ በኋላ በዛሬው ዕለት በከተማ ደረጃ በተካሄደው የማጠቃለያ ውድድር 86 ሰልጣኞች በ20 የሙያ አይነቶች ውድድር አድርገዋል።
.