የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ትብብር ወደ አገራዊ ምርምር ተሸጋገረ።
ግንቦት 10/2018 ዓ.ም
የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የተለመዱ አሰራሮችን በመስበር የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማትን ጨምሮ የኢንተርፕራይዞችን እውነተኛ ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ስራዎችን ወደ ማምረት ተሸጋግሯል።
ይህ የኮሌጁ አዲስ የለውጥ አቅጣጫ ከንድፈ-ሀሳብ ባለፈ መሬት ላይ የወረደ እውነተኛ ማሳያዎችን ማስመዝገብ መቻሉን የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንተርፕራይዝ ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ጋር የተደረገው የቴክኖሎጂ ትብብር ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ወጪውን ሙሉ በሙሉ በመሸፈን በ130,000 ብር ያስገነባውና በአሁኑ ወቅት አራት ዶክተሮች የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸውን እያከናወኑበት የሚገኘው ዘመናዊ የካርቦናይዘር ወይም የከሰል መስሪያ ማሽን፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለከፍተኛ ምርምር ማዕከላት አስተማማኝ አጋዥ መሆን እንደሚችሉ በተግባር አሳይቷል።
ስለ ማሽኑ የአሰራር ሂደትና ጠቀሜታ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት የኮሌጁ የቴክኖሎጂ ባለሙያ አሰልጣኝ ኃይለየሱስ ወንደሰን እንደገለጹት ይህ የፈጠራ ውጤት ባህላዊውንና ለአካባቢ ብክለት የሚዳርገውን የከሰል አሰራር ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው።
ማሽኑ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራት የሚችል ከመሆኑም በላይ ከዛፍ በተጨማሪ እንደ ሰጋቱራ፣ የግብርና ተረፈ ምርቶች እና እንደ እምቦጭ ያሉ አደገኛ አረሞችን ወደ ከሰልነት የመቀየር አቅም አለው።
አሰራሩም የሚወጣውን ጎጂ ጭስ እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድና ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ያሉ ጋዞችን በውሃ ውስጥ በማሳለፍ አካባቢው እንዳይበከል የሚያደርግ ሲሆን በሂደቱ ውሃው ሲፈላ የሚቀረውና "ስለጅ" የሚባለው የዘይት ዝቃጭ ተመልሶ የተፈጨውን ከሰል ለማያያዣነት በማገልገል በሱፐርማርኬት የሚሸጡ ባለ አራት ማዕዘን የክሰል ብሪኬቶችን ለማምረት ያስችላል።
ይህ የፈጠራ ስራ ማንኛውም ሰው ሞዴሉን አይቶ በቤቱ ሊሰራው የሚችል በመሆኑ ቆሻሻን ወደ ሃብት በመቀየር ረገድ ለከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ የገቢ ምንጭ ይፈጥራል።
የኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን ዶክተር ሙሉጌታ አለሙ በበኩላቸው ኮሌጁ ቀደም ሲል ይደረጉ ከነበሩት የተለመዱ ድጋፎች ወጥቶ አሁን ላይ የኢንተርፕራይዞችን ትክክለኛ ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ጉልበትንና ጊዜን የሚቆጥቡ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ማምረት መሸጋገሩን ያረጋግጣሉ።
ኮሌጁ ጥናቶችን በማካሄድና የባለሙያዎችን ቡድን ወደ ኢንተርፕራይዞች በመላክ ችግሮችን በተግባር የሚፈቱ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም መሰረት በእጅ የሚሰሩ አድካሚ ስራዎችን ወደ ማሽን በመቀየር ረገድ በአንድ ማኑዋል ጠረጴዛ ላይ ረጅም ሜትር የሚሸፍኑ ጨርቆችን ለመቁረጥ እስከ 16 የሚደርሱ ባለሙያዎች በጉልበት ይጎትቱ የነበረውን አሰራር በማሽነሪ እንዲተካ ተደርጓል።
በተጨማሪም የሳሙና ጥሬ ዕቃዎችን በበርሜል በእጅ እየገለበጠ በከፍተኛ ስቃይና ድካም ሲያደባልቅ የነበረውን ኢንተርፕራይዝ አሰራር ለመቀየር ባለ 3 እና ባለ 4 በርሜል የመያዝ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ማሽኖች ተሰርተውለታል።
ዶክተር ሙሉጌታ አለሙ አክለውም እንደገለጹት ኮሌጁ በአዲሱ የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ መሰረት የከተማ ግብርናን ውጤታማ ለማድረግ አራት ወሳኝ ማሽኖችን በተሳካ ሁኔታ ሰርቶ አጠናቋል።
እነዚህም በአንድ ጊዜ እስከ 360 ጫጩቶችን መፈልፈል የሚችልና የሙቀት መጠንን ራሱ መቆጣጠር የሚችል የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማሽን ለእንስሳት የሚሆን የተመጣጠነ መኖን በፎርሙላ መሰረት በአንድ ጊዜ አቀናብሮ ማውጣት የሚችል የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን፣ ለከብቶች የሚሆኑ ግብዓቶችን በጥሩ ሁኔታ ከታትፎና አልስልሶ ለምግብነት ምቹ የሚያደርግ ቾፐር ማሽን እና ምርታማ የሆኑ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ናቸው።
በጠቅላላው በአይሲቲ፣ በአገር በቀል ዕውቀት እና በምርት ማምረቻ ዘርፎች ወደ 16 የሚጠጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለው ኮሌጁ ለመምህራንና ለባለሙያዎች የደረጃ ዕድገትን ከፈጠራ ስራዎቻቸው ጋር በማገናኘት የስራ ተነሳሽነትን በመፍጠሩና አሰልጣኞች እውቀታቸውን በተግባር ለማሳየት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት በመሆኑ፣ የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ ያሳየው ይህ ተሞክሮ ለሌሎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አርአያ የሚሆንና አገራዊ የፈጠራ አቅምን ለማሳደግ ትልቅ አቅጣጫ ጠቋሚ ነው።
.