Welcome to
Home በታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ስም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተሰየመ።

በታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ስም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተሰየመ።

03rd February, 2026

በታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ስም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተሰየመ።

 ጥር 23/2018 ዓ.ም 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በቀድሞ መጠሪያው የአዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በታላቁ የሀገር አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ስም  እንዲጠራ መወሰኑን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የስያሜ ለውጡን በይፋ የማብሰሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።

በማብሰሪያ መርሀ ግብሩ አባት እና እናት  አርበኞችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የአርበኞች ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የአርበኛውን የታሪክ ሚናና ለአገር ነፃነት ያደረጉትን ታላቅ መስዋዕትነት ለማክበር   በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት የተወሰነው ይህ ውሳኔ መንግስት የታሪክ ጀግኖችን ለማስታወስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው ሲሉ  የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ስልጠናና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ ተናግረዋል።

አሁን መሳሪያ ይዘን የምንዋጋው ጠላት የለም ያሉት ኃላፊዋ ትልቁ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ክህሎት በታጠቁ ምርታማ ዜጎች ድል መንሳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የደም መስዋዕትነት ከፍለው ያስረከቡንን ሀገር   ትውልድ የሚያሻግሩ ዜጎችን በመፍጠር የዘመኑን የአርበኝነት ገድል  መፈፀም ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የጀግናው አርበኛ ገድል ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ  ዛሬን የዋጀ የነገን ተስፋ ያሰነቀ ነው ያሉት የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ መስፍን ቸሩ  አርበኛው ህይወታቸውን ሰውተዋል የአሁኑ ትውልድ ደግሞ እራሱን በዕውቀት በማደርጀት  ሀገር ማሻገር ይገባዋል ሲሉ ተደምጠዋል ።

አባት አርበኛ መኮንን መሸሻ በበኩላቸው  ጀግናው በህይወት ዘመናቸው ለሀገር ክብር ከተዋደቁ ጀግኖች መካከል አንዱ መሆናቸውን በመግለፅ ክብራቸውንና ጀግንነታቸው በሚመጥን መልኩ ማሰልጠኛ ኮሌጁ መሰየሙ ደስተኛ መሆናቸው ተናግረዋል።

አርበኛው በንግግራቸው ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ለሀገር አንድነትና ነፃነት ያደረጉትን የታሪክ ገድል ማስታወስ ለወጣቱ ትውልድ ትምህርትና መነሳሳት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ በኮሌጁ የሥራ እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰራተኞች ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን የኮሌጁ የሥራ እንቅስቃሴ በአርበኞች 

ተጎብኝቷል።


.

Copyright © All rights reserved.