‹የኮሌጁ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢንኩቤሽን ማዕከል የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ተግባርና ወደ ገበያ እያሸጋገረ ይገኛል››ዶ/ር ሙሉጌታ አለሙ
ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም
የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ወደ ተግባር በማሸጋገር ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
የኮሌጁ ምክትል ዲን ዶ/ር ሙሉጌታ አለሙ እንደሚሉት ኮሌጁ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ወደ ገበያ እንዲገቡ የቦታ፣ የማሽነሪ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በማመቻቸት ለኢንተርፕራይዞች የጀርባ አጥንት ሆኗል።
በተለይም በአካባቢ ጥበቃና በምግብ ዝግጅት ዘርፍ የተደራጁ ሰልጣኞች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።በኮሌጁ የኢንኩቤሽን ማዕከል ውስጥ ስኬታማ ስራ እየከናወኑ ካሉ ኢንተርፕራይዞች መካከል የሳኮሬጆ ክሎዝ ባግ ዋነኛው ነው።
የድርጅቱ መስራችና የኮሌጁ ሰልጣኝ አብርሃም ተሰማ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትለውን የፕላስቲክ ከረጢት ለመተካት ከጨርቅ፣ ከቃጫና ከድንኳን ጨርቆች የሚሰሩ ጠንካራ ቦርሳዎችን እያመረቱ ይገኛሉ።
"ሳኮሬጆ" የሚለው መጠሪያም "ሳክ" ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃልና "ኮሮጆ" ከሚለው የሀገር ውስጥ ስያሜ የተውጣጣ ሲሆን ምርቱን በመላው ኢትዮጵያ ከማሰራጨት ባለፈ "Made in Ethiopia" በሚል ብራንድ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ትልቅ ራዕይ ሰንቀው እየሰሩ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ኮሌጁ የሰልጣኞችንና የሰራተኞችን የምግብ አገልግሎት ችግር ለመፍታት በሆቴል ዘርፍ ተመራቂዎችን በፈጠራ ስራቸው እንዲደራጁ አድርጓል። በውድድር የተመረጡ አራት የሆቴል ዘርፍ ተመራቂዎች በኮሌጁ ውስጥ በተመቻቸላቸው ዕድል ጥራት ያለው ምግብና የፈጣን ምግብ አገልግሎት እያቀረቡ ይገኛሉ።
ይህም ሰልጣኞቹ የተማሩትን የፈጠራ ክህሎት በቀጥታ ወደ ቢዝነስ እንዲቀይሩና ተጨባጭ የስራ ልምድ እንዲቀስሙ ከማድረጉም በላይ በተቋሙ ውስጥ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት አስችሏል።
የለሚኩራ ማኑፋክቸሪንግ ኮሌጅ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ እነዚህ ተግባራት ወጣቶች ስራ ፈላጊ ከመሆን ወጥተው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
ኮሌጁ በቀጣይም ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን (Green TVET) በማበረታታትና የገበያ ትስስር በመፍጠር የኢንዱስትሪ እድገቱን ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ሙሉጌታ አለሙ ገልጸዋል።

.