🌼 መስከረም 19/2018 ዓ.ም 🌼
ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በየአመቱ በመዲናዋ መከበሩ ለበርካታ ነዋሪዎች የስራ እድል እና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየፈጠረ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኅላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ።
ቢሮው ሀደ ሲንቄዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሃላፊዎች ከ700 በላይ የሚሆኑ የስራና ክህሎት ቢሮ ቤተሰቦች በተገኙበት የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ፤ ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት፣ በብዝሃ ማንነት ብሎም በተፈጥሮ ገፀ በረከት የታደለች መሆኗን አንስተዋል።
ኢሬቻ ከሃገር አልፈው ለዓለም ከሚተርፉት እሴቶቿ መካከል አንዱ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በየአመቱ በመዲናዋ መከበሩ ለበርካታ ነዋሪዎች የስራ እድል እና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
የአብሮነት፣ የእርቅና የምስጋና ባህል እንደመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን ሊጠብቁት እንደሚገባ ተናግረዋል። ከትውልድ ትውልድ እሴቱ ተጠብቆ ይዘልቅ ዘንድም ለትውልዱ አደራ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ማሾ ኦላና በበኩላቸው፤ በዓሉ አንድነትን እያጠናከረና ለሃገር ማንሰራራት መሰረት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።