Welcome to
Home የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዕጩ ተመራቂዎች አዲሱን የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ መሰረት አድርገው የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት አቅደዋል።

የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዕጩ ተመራቂዎች አዲሱን የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ መሰረት አድርገው የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት አቅደዋል።

28th February, 2026

የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ  ኮሌጅ ዕጩ ተመራቂዎች አዲሱን የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ መሰረት አድርገው የራሳቸውን ድርጅት ለመመስረት አቅደዋል።

የካቲት  21/2018 ዓ.ም 

በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አዲሱ ስትራቴጂ ሰልጣኞች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ መስርተው እንዲወጡ የሚያስቀምጠውን ግብ በተግባር እያሳዩ ያሉት የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተመራቂዎች ናቸው።

ወጣት ዲቦራ አብርሃም ከአራት ጓደኞቿ ጋር በመሆን የመሰረቱት ምንትዋብ የተባለ የልብስ ስፌትና ዲዛይን ስራ ፈጠራ ዛሬ በኮሌጁ ውስጥ በኢንኩቤሽን  ማዕከል እየታቀፈ ወደ ተሟላ የቢዝነስ ተቋምነት ለመሸጋገር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ወጣቶቹ ስራውን ለመጀመር ካነሳሷቸው ምክንያቶች አንዱ በገበያ ላይ የሚታየው የአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች ክልከላ አዋጅ ነው። 

ምርቶችን ለደንበኞች ሲያቀርቡ በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ፕላስቲኮችን ከመጠቀም ይልቅ ለአካባቢ ተስማሚና ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ዕቃ መያዥ ከረጢቶችን በራሳቸው ዲዛይን ማዘጋጀት እንደሚችሉ በማመናቸው ስራውን በቁርጠኝነት ጀምረዋል። 

ይህም ውበትን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማጣመር በፋሽኑ ዘርፍ አዲስ ፈጠራ ይዘው እንዲመጡ አስችሏቸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን ማምረትና መጠቀምን በጥብቅ ይከለክላል። 

አዋጁን በሚቃረን መልኩ ፕላስቲክ ይዞ መገኘትም ሆነ ለገበያ ማቅረብ እስከ 200,000 ብር የሚደርስ መቀጮና እስከ 5 ዓመት ጽኑ እስራት ያስከትላል። 

ወጣት ዲቦራና ጓደኞቿ ይህንን አዋጅ እንደ ትልቅ ዕድል በመመልከት ፕላስቲኮችን የሚተኩ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የጨርቅ ግብአቶችን ከምርቶቻቸው ጋር በማጣመር አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛል።

ወጣቶቹን ከሃሳብ ጀምሮ በመደገፍና ተገቢውን የስራ ቦታ በማመቻቸት ረገድ የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ሸለማ ንጉሱ እንደገለጹት ኮሌጁ ሰልጣኞች ተመርቀው ስራ ከመፈለግ ይልቅ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የሌሎችንም የስራ ዕድል እንዲያመቻቹ ሰፊ የኢንኩቤሽን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

አቶ ሸለማ አክለውም እንደ እጩ ተመራቂዎች ያሉ ስራ ፈጣሪዎች አገራዊ አዋጆችን አክብረውና የገበያ ክፍተቶችን ለይተው እንዲሰሩ ኮሌጁ የቴክኒክና የሞራል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምንትዋብ  የሚለው ስያሜ ትርጓሜው ሴቶችን ማስዋብ እንደመሆኑ ወጣት ዲቦራና አራት ጓደኞቿ ጥራት ያላቸውንና ማራኪ የሴቶች አልባሳት በአገር ውስጥ በማምረት የሀገር ውስጥ ብራንድ የመሆን ትልቅ ራዕይ ሰንቀዋል።

ከዚህም ባለፈ ድርጅቱ ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጥና በኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ ቀዳሚ የሆነ ፕላስቲክ አልባ  የቢዝነስ ማዕከል ለመሆን በትጋት እየሰራ ይገኛል።

.

Copyright © All rights reserved.