Welcome to
Announcement "የፈጠራ አቅም ቴክኖሎጂ ልህቀት" የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶችን ለእይታ አቀረበ

"የፈጠራ አቅም ቴክኖሎጂ ልህቀት" የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶችን ለእይታ አቀረበ

23rd April, 2026

"የፈጠራ አቅም ቴክኖሎጂ ልህቀት" የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፈጠራ ውጤቶችን ለእይታ አቀረበ 

አዲስ አበባ | ሚያዝያ 15/ 2018 ዓ.ም

በከተማ አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን 16ኛውን የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ምክንያት በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተፈበረኩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለእይታ አቀረበ። ይህ ኩነት በዘርፉ የተቀረጸውን አዲሱን "ማርሽ ቀያሪ" ስትራቴጂ እና የ 11 DNAs እሳቤዎችን በተግባር ያሳየ መሆኑ ተገልጿል። 

የመንግሥትና የግል አጋርነት (PPP) ለተቋማዊ ሽግግር

የተቋሙ ዋና ዲን አቶ ተስፋዬ አድማሱ በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዛሬ ለታየው ተቋማዊ መነቃቃት መሠረት ሆኗል። ኮሌጁ የኩባንያዎች መፈልፈያ (Incubation Center) እንዲሆንና ወደ ራስ ገዝነት (Autonomy) የሚደረገውን ጉዞ ለማፋጠን የውስጥ ገቢን የማሳደግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተተገበረ ይገኛል። 

ዲኑ አክለውም፣ ይህ ኤግዚቢሽን ከመንግሥትና የግል አጋርነት (PPP) አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ኢንዱስትሪዎችና ኩባንያዎች በኮሌጁ የተሰሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጎብኘት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ (Fabrication) የሥራ ትስስር ስምምነት እንዲያደርጉ የ"አብረን እንሥራ" ጥሪ አቅርበዋል። 

የሕይወት አድን ፈጠራ፦ የባዮ ሜዲካል "Infant Incubator"

የኮሌጁ የልህቀት ማእከል (Center of Excellence) የሆነው የባዮ ሜዲካል ዘርፍ አሰልጣኝ ዩሱፊ አብዱልሃሚድ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የጨቅላ ሕፃናት ማቆያ ማሽን (Infant Incubator) ፈብርኮ ለእይታ አቅርቧል። 

ተነሳሽነት፦ በሀገራችን በማሽን እጥረት ምክንያት የሚሞቱ ሕፃናትን ቁጥር ለመቀነስና ከውጭ የሚገባውን ውድ ማሽን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተሰራ ነው። 

ጥራት፦ ማሽኑ ከማኑፋክቸሪንግና ከአውቶሞቲቭ ክፍሎች ጋር በቅንጅት የተሰራ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ አሁን ላይ ከገለልተኛ ተቋማት የሚሰጠውን የጥራት ማረጋገጫ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። 

"ክህሎት ከዳቦ በላይ ነው"፦ ተግባራዊ የፈጠራ ውጤቶች

በማኑፋክቸሪንግ ዲፓርትመንት አሰልጣኝ ሄኖክ ጎይቶም እና ቡድኑ የቀረበው "Mini Oven" ሌላኛው የኤግዚቢሽኑ ድምቀት ነበር። 

ቢዝነስ መነሻ፦ ይህ ማሽን በዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል (2000 Watt) እና በሶላር የሚሰራ ሲሆን፣ ዳቦን በ10 ደቂቃ ውስጥ መጋገር ይችላል። ከ300,000 ብር በላይ የሚጠይቁ የውጭ ማሽኖችን መግዛት ለማይችሉ ጀማሪ ሥራ ፈላጊዎች እንደ አማራጭ የቀረበ የፈጠራ ውጤት ነው። 

የሪፎርሙ ማሳያ የሆኑ የDNA አውታሮች

በዕለቱ ለእይታ የቀረቡት ሥራዎች የሚከተሉትን የDNA እሳቤዎች ያንጸባርቃሉ፦ 

የኢንተርፕራይዘሽን DNA፦ ኮሌጁ ቴክኖሎጂዎችን ለገበያ በማቅረብ የውስጥ ገቢውን የማሳደግ አቅሙን አሳይቷል። 

የጥራትና ስታንዳርድ DNA፦ የፈጠራ ውጤቶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃን ተከትለው የተሰሩ ሲሆን፣ የሙያ ደረጃቸውን የሚያረጋግጡ የምስክር ወረቀቶችን ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው። 

የአሠራር ልህቀት፦ በአሰልጣኝና ሰልጣኝ ቅንጅት የተሰሩ ሥራዎች የተቋሙን የማምረት አቅም ወደ አዲስ ከፍታ አሸጋግረዋል።

በኤግዚቢሽኑ በራሳቸዉ አቅም የተፈጠሩ  የተለያዩ ዳታ ሲስተሞች ለመረጃ አያያዝ እና አገልግሎት የሚዉሉ፤ ስሞክ ሳከር smoke sucker. ፤(የጭስ ማስወገጃ)፤ ቶይ ፊሊንግ (Toy Filling) ፤ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችና የተለያዩ አልባሳት ስራዎች ቀረበዉ ተጎብኝተዋል፡፡ 

የተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተስፋዬ አድማሱ እንዳረጋገጡት፤ ይህ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ተቋሙ የታለመውን ሀገራዊና ከተማዊ ራዕይ በብቃት ለመወጣትና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት ያረጋገጠበት መድረክ ሆኖ ተጠናቅቋል። 

.

Copyright © All rights reserved.