የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ በወርክሾፖች የፈጠረው አዲስ ተስፋ
መጋቢት 17/ 2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ አራቱ አንጋፋ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች (ተግባረዕድ፣ አቃቂ፣ ልደታ እና ጎፋ) በጋራ ያሳዩት የክህሎት ውጤት፣ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ከሰነድ ባለፈ ወደ ተግባር መሸጋገሩን ያበሰረ ክስተት ሆኗል። "የሀገር በቀል እውቀትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትስስር ለዘላቂ ልማት" በሚል መንፈስ የተከናወነው ይህ ዝግጅት፣ ኮሌጆች ከኢንዱስትሪ አጋሮች ጋር በመሆን ችግር ፈቺ ዜጋን እያፈሩ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
1. የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ፦ የቴክኖሎጂና የኢንተርፕራይዞች አለኝታ
ሰልጣኞች የሰሯቸውን ውጤቶች እና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ የሚያሳዩበትን ይህንን እንቅስቃሴ በዋናነት ያስተባበረው የጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ፣ የአካባቢውን ፀጋ መሠረት ያደረጉ ስልጠናዎችን በማስፋፋት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑ ተመስክሮለታል። የኮሌጁ ዋና ዲን ዶክተር አሸብር ተክሌ እንደገለጹት፣ ኮሌጁ በአውቶሞቲቭ፣ ጋርመንት፣ ሌዘር፣ ጀነራል ማኑፋክቸሪንግ እና ፋርኒቸር ዘርፎች ከ800 በላይ መደበኛና በአመት ከ20,000 በላይ በአጫጭር ስልጠና ዜጎችን በማብቃት ላይ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴ የስትራቴጂውን "Demand-Led Training" (በፍላጎት የሚመራ ስልጠና) እሳቤ በተግባር የገለጸ ነው።
2. ስልጠና ከዳቦ በላይ፦ የሰልጣኞች ድምፅ ከወርክሾፕ እስከ ገበያ
ምርትና ፈጠራቸውን ያስተዋወቁ ሰልጣኞች፣ ስልጠናው ከቴክኒክ ሙያ ባለፈ የአስተሳሰብ ለውጥ (Mindset Shift) ማምጣቱን ይናገራሉ።
የፈጠራ ባለቤቱ ህኖክ ጎይቶም፦ በGIZ ድጋፍና በተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ባገኘው የ6 ወር ስልጠና የፈጠራ አቅሙን አሳድጓል። "በተለይ በ3D Drawing የወሰድኩት ስልጠና ውስጤ የነበረውን ስራ ፈጠራ አውጥቶታል፤ አሁን ኦቨንና የስፖርት ማሽኖችን ሰርተናል" ይላል። ወደፊትም እነዚህን ምርቶች በፀሐይ ኃይል (Solar) እንዲሰሩ በማድረግ የገጠሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት ራዕይ ሰንቋል። ይህም ስልጠናው "ችግር ፈቺ" ባለሙያ እያፈራ መሆኑን ያሳያል።
ኢቫና አሰፋ (የፋሽን ዲዛይነር)፦ ከአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰልጣኝ የሆነችው ኢቫና፣ በዲግሪ ተመርቆ ስራ ፈላጊ ከመሆን ይልቅ፣ ቴክኒክና ሙያ የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ እንዳስቻላቸው ትናገራለች። "ማህበረሰቡ ለቴክኒክና ሙያ ያለው አመለካከት ተቀይሯል፤ Skill ይዞ መውጣት ከወረቀት ዲግሪ እንደሚሻል ተረድቷል" በማለት "Training Beyond Bread" የተሰኘውን እሳቤ ትመሰክራለች።
3. ማህበራዊ ትስስርና የኢንኩቤሽን ውጤቶች
ስትራቴጂው ተቋማት የኩባንያዎች መፈልፈያ (Incubation Centers) እንዲሆኑ ያዛል። ገነት አበበ እና ጓደኞቿ ከጎፋ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ከቤት እመቤትነት ወጥተው በ6 ወር ስልጠና አሁን ላይ የወንዶች ፓንት በብዛት እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ። "ግማሻችን ገበያ በመፈለግ፣ ግማሻችን በማምረት ተራ በተራ እየሰራን ራሳችንን ችለናል" የሚሉት ገነት፣ የመስሪያ ቦታ ቢመቻችላቸው ይበልጥ ለማደግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ማጠቃለያ፦ የስትራቴጂው ስኬት በመሬት ላይ
ዝግጅቱ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ዝም ብሎ ሰነድ ሳይሆን፣ የዜጎችን ሕይወት እየቀየረ ያለ ሕያው እንቅስቃሴ መሆኑን አረጋግጧል። በዲጂታይዜሽን (እንደ 3D ስልጠና)፣ በጠንካራ አጋርነት (እንደ GIZ ድጋፍ) እና በአስተሳሰብ ለውጥ የታጀበው ይህ ሽግግር፣ ሀገራችን ለምትመኘው የኢንዱስትሪ ልማት የጀርባ አጥንት መሆኑ አልቀረም።

.