የዓለም ባንክ ልዑክ በአዲስ አበባ የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና የሥራ ፕሮጀክት እንቅስቃሴ ጎበኘ።
ጥር 16/2018 ዓ.ም
በዓለም ባንክ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዋንሳይ ዥንግ የተመራ የልዑካን ቡድን የአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔትና የሥራ ፕሮጀክት የስራ እንቅስቃሴዎችን በመጎብኘት ምልከታ አድርጓል።
የልዑካን ቡድኑ ለተጨማሪ ገቢ ማስገኛ የሚያገለግሉ የከተማ ግብርና ስራዎች፣ የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብሮች እንዲሁም ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የተሸጋገሩ የከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የሥራ እንቅስቃሴዎችን ተመልክቷል።
በዚህ ወቅት የዓለም ባንክ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ዋንሳይ ዥንግ ፕሮጀክቱ ለወጣቶችና ለተጋላጭ ማህበረሰቦች የክህሎት ልማትና ስልጠና ላይ ትኩረት እየሰጠ መሆኑ በዜጎች የወደፊት ሕይወት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የአቅም ግንባታ፣ የክህሎት ልማትና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ በማካተት መተግበሩ ከተረጂነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጠንካራ መሠረት መሆኑን አመልክተዋል። ይህም ስኬት የፌዴራልና የከተማ መንግሥታት ጠንካራ አመራርና ከዓለም ባንክ ጋር ያለው ትብብር ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ፕሮጀክቱ በ88 የሀገሪቱ ከተሞች ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸው፣ ዜጎች ተቀምጠው የሚደገፉበት ሳይሆን እንደየ አቅማቸው እየሰሩ ጥሪት የሚፈጥሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከለውጡ ወዲህ ለከተሞች ዕድገት በተሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ከተሞች የሥራ አጥነትና የድህነት ማሳያ ከመሆን ወጥተው የብልፅግና ማሳያ እንዲሆኑ በሚደረገው ጥረት ፕሮጀክቱ የጎላ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተመዘገበው ይህ ስኬታማ አፈፃፀም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመተግበር ጥሩ ማሳያ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ድህነትና ሥራ አጥነትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች የክህሎት ባለቤት ሆነው በዘላቂነት እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እቴማር ጌታቸው ፕሮጀክቱ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ዜጎች በመደገፍ ረገድ አዎንታዊ ተፅዕኖ እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በምልከታው የኢፌዴሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን ጨምሮ የዓለም ባንክ፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ወ/ሮ ማርያም ሳሊም፣ የዓለም ባንክ ተወካዮችና የፌዴራልና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


.