የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የስልጠና ተደራሽነትና አግባብነት በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ ሰልጣኞች ለገበያው የማቅረብ ዓላማ እንዳለው የታመነበት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ለመተግበር የሚያስችል ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የአሰልጣኞች የዝውውርና የምደባ አፈፃፀም ደንብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በስትራቴጂው መሰረት በከተማዋ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የአካባቢ መልማት ፀጋቸውን መሰረት አድርገው በክላስተር አደረጃጀት ተዋቅረዋል።
በዚህም የልል እና የቴክኒካል ክህሎት የሚሰጡ አሰልጣኞችን ከስልጠና ፍላጎት እና ከማሰልጠኛ ክፍሎች ጋር የማጣመር ስራ የተሰራ ሲሆን በቅርቡ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በወጣው ደንብ መሰረት የስልጠና ክፍላቸው የሚታጠፉ አሰልጣኞች የማዘዋወር ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል።
አሰልጣኞችን ከማዘዋወር ባሻገር የሚታጠፉ ሙያዎች ላይ ያሉ ሰልጣኞች ስልጠናው ወደሚሰጥበት ክላስተር ኮሌጅ ተዘዋውረው ስልጠናቸውን እንደሚከታተሉ ተጠቅሷል።
ተግባራዊ በሚደረገው የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ መሰረት 70 በመቶ የሚሆነውን በዞኒንግና ዲፈረንሼሽን መሰረት የሰልጣኝ ቅበላ የሚካሄድ ሲሆን 30 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ የጋራ ኮርሶች እንደሚሆኑ ተመላክቷል።
የዞኒንግና ዲፈረንሼሽን ስትራቴጂ ትግበራው የበቃ አሰልጣኝ በመፍጠር ብቃት ያለው አሰልጣኝ ለገበያው ለማቅረብ ያስችላል ያሉት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የውጤት ተኮር ስልጠናና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማ ስትራቴጂው የአዲስ ሰልጣኝ ቅበላ ከመካሄዱ በፊት ይተገበራል ብለዋል።ስትራቴጂው የአሰልጣኝ ሰልጣኝ እንዲሁም የስልጠና ክፍል ጥምርታውን በማመጣጠን ዘርፉ ለሀገር እድገትና ብልፅግና የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችላል ሲሉ ጨምረውም ገልጸዋል።በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ #አቶ መሀመድ ልጋኒ በበኩላቸው የስትራቴጂው መተግበር የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፉን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራውን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የኮሌጆችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።በውይይቱ ለቢሮው ተጠሪ የሆኑ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ዲኖችን ጨምሮ የመምህራን ማህበር ተወካዮችና የሰው ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።
.