5ኛው ከተማ አቀፍ የክህሎት ውድድር በኮሌጅ ደረጃ በምስራቅ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በይፋ ተጀመረ።
የካቲት 4/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችል የክህሎት አቅም ለመገንባትና የሰልጣኞችን የተግባር ብቃት ለመፈተሽ ያለመው የ16ኛው ቴክኒክና ሙያ ሳምንት አካል የሆነው 5ኛውን የከተማ አቀፍ የክህሎት ውድድር ዛሬ በኮሌጅ ደረጃ በምስራቅ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በይፋ አስጀምሯል።
የ2018 በጀት ዓመት የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የክህሎት ውድድር ላይ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከርና በዘርፉ ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አቅም የማምረት ባህልን ለማጎልበት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። ውድድሩ በተለይም በሙያ ደረጃ 3 እና 4 ላይ የሚገኙ ሰልጣኞች ያላቸውን መሰረታዊ የክህሎት ብቃት የሚፈትሹበትና በመካከላቸውም የተወዳዳሪነት መንፈስ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።
ውድድሩ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብና ብቃት ያላቸው ሰልጣኞች ጎልተው የሚወጡበት መሆኑን የገለጹት በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ ውድድሩ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ቴክኖሎጂን እንደ ዋና አማራጭ በመጠቀም ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት ያለመ ነው ብለዋል።
አገሪቱ በቴክኖሎጂ አብዮት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ መፍጠርና መፍጠን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜም "መዝለል" እንደሚገባ አቶ ሜዴቅሳ አሳስበዋል።
አሁን ላይ አለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ብቻ ከመኮረጅ ባለፈ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅ ለነገው ትውልድ የምትተርፍ አገር ለመገንባት ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህ ውድድርም ሰልጣኞች በመካከላቸው ጤናማ ፉክክር በማድረግ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት በከተማዋ በሚገኙ 14 የመንግስት ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በተጀመረው የሰልጣኞች የክህሎት ውድድር 509 አሰልጣኞች በ20 የሙያ አይነቶች የሚወዳደሩ ይሆናል።
በኮሌጅ ደረጃ የተጀመረው ውድድር እንደተጠናቀቀ አሸናፊ የሆኑ ሰልጣኞች በክላስተር እንዲሁም በከተማ ደረጃ አሸናፊዎች እውቅና እንደሚያገኙ ተገልጿል።

.