Welcome to AATVETB College
Announcement "ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ስልጡን አመራር፤ የምርታማነትና የልህቀት ማዕከል የስትራቴጂክ ስልጠና ማጠቃለያ

"ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ስልጡን አመራር፤ የምርታማነትና የልህቀት ማዕከል የስትራቴጂክ ስልጠና ማጠቃለያ

24th June, 2026


🇪🇹ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም🇪🇹

ቢሾፍቱ (ደብረዘይት)፦ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራትንና የዘርፉን የአመራር አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፤ የአመራር ክህሎትን በማሳደግ ተቋማዊ ተወዳዳሪነትን እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ያለመ የ"ስትራቴጂክ ሊደርሺፕ" (Strategic Leadership) ስልጠና በስኬት ተጠናቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የምርታማነትና የልህቀት ማዕከል ዋና አዘጋጅነት ሰኔ 14/2015 ዓ.ም የተጀመረው ይህ የአቅም ግንባታ መርሃ-ግብር፤ በጥናት በተለዩ የአመራር ክፍተቶች መነሻነት የተዘጋጀ ነው። ስልጠናው ይበልጥ ውጤታማ እና ተደራሽ እንዲሆን በሁለት ዙር ተከፍሎ የተሰጠ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና ለ45 ሰልጣኞች በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት ደግሞ  የሁለተኛው ዙር ለ 39 ሰልጣኞች ስልጠና በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን፤ በስትራቴጂክ ሊደርሺፕ (Strategic Leadership)፣ በቼንጅ ማኔጅመንት (Change Management) እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን (Digital Transformation) ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። በሁለቱም ዙሮች የመድረኩ ተሳታፊዎች የኮሌጅ ዲኖችና ምክትል ዲኖች፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመጡ ተወካዮች እንዲሁም የቢሮው የዘርፉ የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች ነበሩ።
የማዕከሉ ምክትል ዲን አቶ መክብብ አሰፋ በሰጡት መረጃ፣ ተቋማት አመራሩን ስለሚመስሉ የታዩትን የአመራር ክፍተቶች በጥናት ለይቶ ይህንን ስልጠና ማዘጋጀት ማስፈለጉን ገልጸው፤ ማዕከሉ በሁለት ዙር ይሄን መድረክ በኃላፊነት መምራቱንና ወደፊትም የክትትልና የአፈጻጸም ግምገማ (Impact Assessment) ስራዎች እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።
በማጠቃለያው መርሃ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት በቢሮ ሃላፊ ደረጃ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የኢንተርፕራይዝና የቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሜዲቅሳ ከበደ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ፈጣን እድገት የምታሳይ "ስማርት ሲቲ" በመሆኗ ይህንን ፈጣን እድገት መሸከም የሚችል ተወዳዳሪ መሪ ማፍራት ግድ ይላል ብለዋል። "ትላንት በነበረን ክህሎት እና ልምድ ብቻ ቆመን ነገ ተወዳዳሪ መሆን አንችልም" ያሉት አቶ ሜዲቅሳ፣ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ወደ ተቋሞቻቸው በመውሰድ በተግባር ሊለውጡትና እራሳቸውን በየጊዜው ሊያዘምኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቢሮ ሃላፊ ደረጃ ምክትል ቢሮ ሃላፊና ዉጤት ተኮር ስልጠና እና  ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት  ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ በማጠቃለያው መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የምርታማነትና የልህቀት ማዕከል የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት በትግል ውስጥ እያለፈ እያከናወናቸው ያሉትን ስኬታማ ስራዎች አድንቀዋል። ቢሮውም ተቋማዊ መዋቅሩ እንዲሻሻልና የአመራሩ ዓቅም እንዲገነባ ሙሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ዳግማዊት አክለውም፣ በአሁኑ ወቅት በ14ቱ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ውስጥ ከ55 ሺህ በላይ ተማሪዎች (ትውልድ) እንደሚገኙ ጠቁመው፣ "ይህ ትውልድ ከእኛ ይልቅ በቴክኖሎጂው ረገድ የገፋ (Advanced) ስለሆነ፣ እኛ መራመድና እራሳችንን ማሻሻል ካልቻልን ጥሎን ይሻገራል፤ ስለዚህ እራሳችንን ከዘመኑ ጋር ማዘመንና ሼፕ ማድረግ ይጠበቅብናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
ስልጠናውን በንቃት የተከታተሉት የአቃቂ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ፀጋዬ ዱኛ እና የአሰልጣኝ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተክለወይኒ ወልደጊዮርጊስ፣ ስልጠናው ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ፣ በተለይም በአዲስ አበባ የተጀመረውን የ"ዞኒንግ እና ዲፈረንሼሽን" አሰራር ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ይህ አመራሩ የወደፊት ዕቅዶችን በስትራቴጂክ እይታ እንዲመራ፣ ተቋማዊ ለውጦችን በብቃት እንዲያስተዳድሩ እና በየደረጃው ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ታስቦ የተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና፣  ስልጠናዉን ላጠናቀቁ  አመራሮች  የሰርተፍኬት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት በመከናወን በደመቀ ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል።

.

Copyright © All rights reserved.